ሕብረት ባንክ አ.ማ. እና ማስተር ካርድ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

ሕብረት ባንክ አ.ማ እና ማስተር ካርድ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ/ም በሕብረት ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ ማስተርካርድ በተቀመጡ መመዘኛዎች መሰረት ለባንኩ የማማከርና እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ሕብረት ባንክ የሚሰጣቸውን የካርድ ባንኪንግ አገልግሎቶች ለማስፋፋትና ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሕብረት ባንክ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት የባንኩ ተ/ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፅጌረዳ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራችን የፋይናንስ ዘርፍ እየመጡ ያሉትን ለውጦች ባገናዘበ መልኩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ አሰራሮችን መከተል ግድ መሆኑን ባንኩ እንደሚገነዘብ እና ለዚህም ስትራቴጂ ቀርጾ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ አክለውም እንዲህ ያሉ በጋራ ስኬት ላይ የተመሰረቱ አጋርነቶች ለበለጠ ውጤታማነት ትልቅ አሰተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ ገልጸው ማስተርካርድ ለሚያደርገው ድጋፍ እና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የማስተርካርድ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሚስተር ማርክ ኤልየት በበኩላቸው ማስተር ካርድ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ፔይመንት አገልግሎትን እንዲጠቀሙ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ሕብረት ባንክ በዚህ ረገድ ያሳየው ፍላጎት እና ተነሳሽነት የሚበረታታ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ የሕብረት ባንክና የማስተር ካርድ ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡

ሕብረት ባንክ
በሕብረት እንደግ!

Similar Posts